በፕሪቶሪያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት ተግባራዊነት የበኩላቸውን ሚና እንደሚጫወቱ የድፌንድ ኢትዮጵያ ዩኬ ግብረ ሀይል አባላት አስታወቁ
የግብረሀይሉ አባላት ሁለተኛ አመት የምስረታ በአላቸውን በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባከበሩበት ወቅት የተፈረመው የሰላም ስምምነት እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡
በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጰያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተፈሪ መለሰ በወቅቱ እንደተናገሩት ባለፉት ሁለት አመታት ኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ የውጪ ሀይሎች ከፍተኛ ጫና ለመፍጠር የሚያደርጉትን የተቀናጀ ጥረት ለመቋቋም በዩናይትድ ኪንግደምና አየርላንድ በሚኖሩ ኢትዮጰያዊያንና ት/ኢትዮጰያዊያን አማካይነት “ኢትዮጵያን እንታደግ “ በሚል ግብረሀይሉ መመስረቱን አስታውሰዋል፡፡
ግብረሀይሉ ለኢትዮጰያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ቤተሰቦች ና በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ ከማድረግ ጎን ለጎን የወደሙ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት በሚደረገው ሀገራዊ ጥረት የበኩሉን ድጋፍ ማድረጉን የተናገሩት አምባሳደር ተፈሪ ሀገራችን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በነበረችበት ወቅት በዲፕሎማሲ ፣ በሚዲያ ፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ እና በሎቢ ራሱን በማደራጀት እና ከሌሎች የኢትዮጰያ ኮሚኒቲዎች ጋር በመተባበር የአደባባይ የተቃውሞ ሰልፎችን በመጥራት በዩናይትድ ኪንግደም አዎንታዊ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል፡፡
በተፈረመው የሰላም ስምምነት ዙሪያ ለግብረሀይሉ አባላት ሰፊ ማብራሪያ የሰጡት አምባሳደር ተፈሪ የሰላም ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን እንደወትሮው አባላቱ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ጠይቀዋል፡፡
አክለውም የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ እየተደረገ ጎን ለጎን የኢትዮጵያን መልካም ገጽታዎች ለአለም የምናስረዳበት ፣ በንግድ ፣ በኢንቨስትመንት ፣ በቱሪዝምና ለኢትዮጰያ ምርቶች ገበያ ለማፈላለግ እንደ ከዚህ ቀደሙ በነበረው ኢትዮጵያን የመታደግ መርህ በአንድነት በመነሳት የበለጠውን ስራ የምንሰራበት ጊዜው አሁን ነው ብለዋል፡፡
የግብረሀይሉ አባላት ላደረጉት አስተዋጽኦ በመንግስትና በራሳቸው ስም ከፍተኛ ምስጋናም አቅርበዋል፡፡
የድፌንድ ኢትዮጵያ ዩኬ ግብረ ሀይል አስተባባሪ አቶ ዘላለም ተሰማ በበኩላቸው የሰላም ስምምነቱ ለኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ መሰረት የሚጥል ውሳኔ ነው በማለት ባለፉት ሁለት አመታት የኢትዮጵያን ድምጽ በአለም አደባባይ ለማሰማት ለወጡ በዩናይትድ ኪንግደምና አየርላንድ ነዋሪ ለሆኑ ኢትዮጵያዊያን ፣ ት/ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጅ ለሆኑ የውጪ ዜጎች ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
አቶ ዘላለም አያይዘውም ኢትዮጵያ ችግር ውስጥም ሆና በርካታ የልማት ስራዎችን ስታከናውን እንደቆየች አስታውሰው የሰላም ስምምነቱ እነዚህን የልማት ስራዎች ይበልጥ ለማከናወን እድል የሚሰጥ በመሆኑ ከእንግዲህ ለልማት በሚደረገው ሀገራዊ ጥረት የግብረሀይሉ አባላት ሙሉ አቅማቸውን ለዚህ ተግባር እንደሚያውሉ ተናግረዋል፡፡
በእለቱ ለግብረሀይሉ አባላት የምስጋናና የምስክር ወረቀት አሰጣጥ ስነስርአት ተካሂዷል፡፡
Latest News
Browse allwe appreciate your help.