ክቡር አምባሳደር ተፈሪ መለሰ በዌስት ሚኒስቴር የሁሉም ፓርቲዎች ፓርላሜንታዊ ቡድን አባላትና እንግዶች በተገኙበት ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ እንደዚሁም ስላሉት የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ዕድሎች ገለፃ አድርገዋል
በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር ክቡር ተፈሪ መለሰ በዌስት ሚኒስቴር የሁሉም ፓርቲዎች ፓርላሜንታዊ ቡድን አባላትና እንግዶች በተገኙበት ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ እንደዚሁም ስላሉት የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ዕድሎች ገለፃ አድርገዋል፡፡
በዚሁ ገለፃቸውም በደቡብ አፍሪካ፣ በኬንያና በአገር ውስጥ በተደረጉ ውይይቶች የተደረሱ ስምምነቶችን በመተግበር የተረጋጋና ሠላማዊ ሁኔታ በትግራይ ክልል ከመፈጠሩም በላይ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ከማቅረብ በተጨማሪ የምግብ እህል፣ የህክምና ቁሳቁሶች እንዲሁም የባንክ የኤሌክትሪክና የስልክ አገልግሎቶች በስፋት እየተደረሰ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ በመሆኑም አሁን የተደረሰበት ሠላም የበለጠ እየተረጋገጠ ህዝቡን ወደ መደበኛ ህይወት የመመለስና በጦርነቱ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ የመገንባት ሥራ በትኩረት እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡ በዚህም የእንግሊዝ መንግስትን ጨምሮ የዓለም ህብረተሰብ ድጋፉን እንዲለግስ እንደሚጠበቅ ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያ እጅግ አዋጪ የሆኑ ሠፋፊ የኢንቨስትመንት ዕድሎች በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ አግሮፕሮሰሲንግ፣ በኢነርጂ፣ በጤና፣ በቱሪዝም እና በማዕድን ዘርፎች ያሏት ከመሆኗም በተጨማሪ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫና በአፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅና አውሮፓ ሀገራት ቅርብ ገበያ ናት፡፡ የህዝቧ ብዛት 120 ሚሊዮን እየደረሠ ሲሆን ከ60-70% የሚሆነውም ሠራተኛ ወጣት ኃይል እንደሆነ ተገልጿል፡፡ መንግስት የተለያዩ ሪፎርሞች በመሥራት ሀገሪቱ ለውጪ ኢንቨስትመንትና ንግድ የበለጠ የተመቸ ሁኔታ የተፈጠረባት ሆናለች፡፡ የንግድ ህግ ማሻሻያ፣ የካፒታል ገበያን ለመጀመር የህግ ማዕቀፍና ተቋም መፍጠር፣ የፋይናንስ ዘርፉ የውጪ ባንኮችን ተሣትፎ እንዲያካትት መደረግ፣ የኢንቨስትመንት ህግን ማበረታቻ ሥርዓት ማሻሻል፣ የቴሌኮም አገልግሎት ለግል ኢንቨስትመንት ክፍት መደረግ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በዚህም የተወሰኑ የእንግሊዝ ኩባንያዎች በተለያዩ መስኮች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት እየተሳተፉ ሲሆን የበለጠ እንዲሣተፉ የእንግሊዝ መንግስትም ማበረታታት እንደሚገባው ለፓርላማ አባላቱ ተገልጾላቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድም መንገደኞችን በ120 አገራት የሚያገናኝ የበረራ መረብ የፈጠረ ሲሆን ዕቃዎችንና ማጓጓዝ በተመለከተ በ60 ሀገራት የካርጎ አገልግሎት ተደራሽ እያደረገ መሆኑ ለባለሀብቶቹና ለንግዱ ማህበረሰብ ተጨማሪ ዕድል መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በመጨረሻም ከተሣታፊዎች መለስተኛ ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ በማጠቃለያም የቡድኑ ሰብሳቢ የፓርላማ አባል የሆኑት ሎርድ ሎረንስ ሮበርትሠንና ሚስተር ቲም ጆንሰን ለኢትዮጵያ ያላቸውን ፍቅር እንደዚሁም ኢትዮጵያ ያላትን ዕድልና እያስመዘገበች ያለችውን የኢኮኖሚ ዕድገት በማንሣት አድናቆታቸውን ገልጸዋል፤ በቀጣይም የንግድ ልዑካን ቡድን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ እንደሚሄድ ገልጸዋል፡፡
Latest News
Browse allwe appreciate your help.